Newsletter Signup

Sign-up to stay in touch with Saint George FC

Reagent/Protectorator
Yidnekatchew Tessema
Mengistu Worku

St. George Gallery

News

Get your latest news from Ethio Premiere. Stay updated with what's happening around the league.

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆላንዳዊውን አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማንን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጠረ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ አመት ለሚጠብቁት የአህጉራዊ እና የውስጥ ውድድሮች ዋናውን ቡድን በአሰልጣኝነት እንዲመሩለት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማንን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡ በዚህም መሰረት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጋር የሁለት አመት የኮንትራት ስምምነት በዛሬው እለት የተፈራረሙ ሲሆን በመጪው ሀምሌ ወር ላይም ቡድናችን ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሰልጠን ስራቸውን የሚጀምሩ ይሆናል፡፡

ማርቲን ኩፕማን የተወለዱት እ.ኤ.አ. በ1956 ጉልደርስ በተባለችው የሆላንድ ግዛት ውስጥ ሲሆን የተጨዋችነት ዘመናቸውንም በጎ ኤሄድ ኤግልስ፤ኤፍ ሲ ቲዌንቴ እና ኤስ ሲ ካምበር ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀሪው የውድድር ዘመን የሚቀሩትን የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በፋሲል ተካልኝ እየተመራ የሚጨርስ ሲሆን ኩፕመንም በመጪው ሀምሌ ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት መንበርን የሚረከቡ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ኩፕማን በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በሀገራቸው እና በተለያዩ የውጭ ሀገራት ተዘዋውረው የሰሩ ሲሆን በተለይም በአፍሪካ የኮንጎውን ታላቅ ክለብ ኤኤስ ቪታ ክለብን ጭምር አሰልጥነዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለአሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን መልካም የስራ ዘመን ይመኝላቸዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስራ አመራር ቦርድ ሆላንዳዊውን ሬኔ ሂድኒክን በማነጋገር ላይ ነው

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስራ አመራር ቦርድ ሆላንዳዊውን ሬኔ ሂድኒክን በማነጋገር ላይ ነው

የቅዱስ ስፖርት ክለብ ደብረዘይት ቀበሌ 01 ውስጥ እያስገነባ ለሚገኘው የይድነቃቸው ተሰማ እግር ኳስ አካዳሚ ውስጥ የሚሰሩ አሰልጣኞችን ለመቅጠር በማወዳደር ላይ የሚገኝ ሲሆን ሆላንዳዊው ሬኔ ሂድኒክም በትናንትናው ዕለት ቢቀጠሩ አካዳሚውን በምን መልኩ ማስተዳደር እንደሚችሉ ለስራ አመራር ቦርድ አባላት አቅርበው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞው የጋና ከ17 አመት በታች እና የሩዋንዳውን ኤፒአር ያሰለጠኑ ሲሆን በሀገራቸውም የኤፍ ሲ ዶርቼት እና ግራፍሻፕ የተባሉ ፕሮፌሽናል ክለቦችን አሰልጥነዋል፡፡
የአሰልጣኙ የአካዳሚ አሰልጣኝነት ቅጥር ያልተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ቀናት በውይይት ከዳበረ በኋላ ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል፡፡

“ የእኛ ምኞት ደጋፊው ከጨዋታ መልስ እየጨፈረ ከስታዲየም እንዲወጣ ነው ” ፋሲል ተካልኝ

ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት እና ዋናው ቡድን ከአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ዘጠናዎቹ አጋማሽ ድረስ ለበርካታ አመታት በቀኝ መስመር ተጨዋችነት እና በአምበልነት ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ለኢትዮጵያ ወጣትና ኦሎምፒክ ቡድንም በበርካታ ኢንተርናሽል ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት ለመጫወት የበቃ ተጨዋች ነው፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብን ወክሎ ይጫወት በነበረበት ዘመንም በበርካታ የሻምፒዮንነት ድሎችን በአምበልነት ለማንሳት የበቃ ተጨዋች ነው፡፡ በተጨዋችነት ዘመኑ በሜዳ ላይ ምርጥ ችሎታው የሚታወቀው ፋሲል ተካልኝ ጫማውን ከሰቀለ በኋላም በቅድሚያ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት ግልጋሎት በመስጠት እስከ መጋቢት 11/2007 ዓ.ም ድረስ ከቆየ በኋላ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ስራውን ጀምሯል፡፡ ይህንንም ምክንያት በማድረግ ተከታዩን ቃለ ምልልስ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- የመጀመሪያውን ዙር የቡድናችንን ውጤት እንዴት ተመለከትከው ?

ፋሲል፡- በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ጥሩ ተጫውተናል ብዬ አላስብም፡፡ ደጋፊው እና ሌላው ሰው ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሚጠብቀው መልኩ እንደ ጊዮርጊስ አልተጫወትንም፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- በቀድሞ ጊዜ በብዙ ጨዋታዎች በዛ ያሉ ግቦችን አስቆጥረን እናሸንፍ ነበር፡፡ አሁን ይህንን ያህል ቁጥር ግብ ቡድናችን ሲያስቆጥር አንመለከትም ለምን ይሆን ?

ፋሲል፡- ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ የተጨዋቾች የአጨዋወት ዘይቤ፣ የሊጉ ደረጃ፣ የአጥቂዎች ብቃትን ያካተቱ ጉዳዮች በጥናት ሊታዩ ይገባል፡፡ ከዚህ ሌላ ግን ተጋጣሚዎቻችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥሙ በተለየ ሁኔታ ተዘጋጅተው መምጣታቸው፣ እኛ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ስለሆንን ብቻ እነሱን በቀላሉ ማሸነፍ እንደምንችል አድርገን ወደ ግጥሚያው መግባታችንም ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአመታት በፊት ቡድኖች እኛን ሲያገኙ ቀድመው ተስፋ ቆርጠው ይገቡ ነበር አሁን ግን ነጥብ ማስጣልን አስበው ነው የሚገቡት እነዚህ ምክንያቶች ሊሆኑ ቢችሉም በጥናት መረጋገጥ አለበት፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- ላንተ ውብ እግር ኳስ ምንድን ነው ?

ፋሲል፡- ውብ እግር ኳስ የሚጫወት ቡድን ኳስን በአግባቡ የሚቆጣጠር እና ቶሎ ቶሎ በማጥቃት የግብ ዕድሎችን በመፍጠርና ግብ አስቆጥሮ ማሸነፍ የሚችል ቡድን ለእኔ ውብ እግር ኳስን ይጫወታል እላለሁ፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- የምትመርጠው የታክቲክ አሰላለፍ ?

ፋሲል፡- በቁጥር ግለፅ ካልከኝ እኔ ቁጥሮች ብዙም አያሳስቡኝም የታክቲክ ምርጫውን ስመርጥ የማስበው ነገር ቢኖር በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ ተጨዋቾችን ባላንስ ያደረገና አጥቅቼ እንድጫወት የሚያደርገኝን አሰላለፍ እመርጣለሁኝ ፡፡ ነገር ግን ታክቲክ እንደ ደሀ ብርድ ልብስ ነው ይባላል፡፡ ጭንቅላትህን ስትለብስ እግርህ ባዶ ይሆናል፡፡ እግርህን ስትለብስ ደግሞ ጭንቅላትህን ባዶ ይሆናል እና ከቁጥሮቹ ይልቅ ለቡድኔ ቅርፅ በጣም እጨነቃለሁ የግድ ምረጥ ካልከኝ ግን 4-3-3 እና 4-2-3-1 እመርጣለሁ፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- ይሄ የፋሲል ቡድን ነው የምንለው መቼ ነው ?

ፋሲል፡- እሱን በጊዜ ወይም በቀን ለመግለፅ ያስቸግራል፡፡ ቡድኑን በውድድር መሀል ነው የተቀበልነው፡፡ ከዝግጅት ጊዜ ጀምሮ ቢሆን በዚህ ቀን ነው ብዬ ልነግርህ እችላለሁ፡፡ አሁን እኛ በምንፈልገው መንገድ እየመከርን፣ እያሰራን እና እያጫወትን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን የኛ የምንለውን ቡድን ለማሳየት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡


 

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- በእግር ኳስ ህይወትህ ውስጥ ካለፉት አሰልጣኞች የትኛው ተፅዕኖ አድርጎብሀል ?

ፋሲል፡- በተጨዋችነትም በምክትል አሰልጣኝነት ዘመኔም ብዙ አሰልጣኞችን ተመልክቼያለሁ ከእያንዳንዱ አሰልጣኞች ጠንካራ ወይም በጎ ነው የምለውን ነገር ወስጃለሁኝ፡፡ ከእያንዳንዱ አሰልጣኝ የተማርኩት ብዙ ነገር አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኳስ መጫወቴ፣ ማየቴ እና ከአሰልጣኞቼ የተማርኩት ነገር ሁል ጊዜም እራሴን እንድመስል የራሴ የሆነ ነገር እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- በዛሬው እለት ከመከላከያ ጋር እንጫወታለን አንተ ደግሞ ለገብረመድህን ጥሩ ስሜት እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ ጨዋታው እንዴት ነው ?

ፋሲል፡- ለገብረመድህን ሀይሌ ትልቅ ክብር እና ፍቅር አለኝ፡፡ በዘመኔ ከተመለከትኳቸው ምርጥ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ከገብረመድህን ጋር በአሰልጣኝነት ተገናኘሁ ብዬ የተለየ ስሜት አይሰማኝም ባለፈው አመትም ተገናኝተን ነበር፡፡  በእለቱ አንድ ተጨዋች ጎሎብን ጥሩ የተጫወትነው እኛ ነን በጨዋታው ጥሩ ቅርፅ የነበረው የዕኛ ቡድን ነበር፡፡ ጨዋታውንም በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ችለን የምንችለውን ሁሉ አድርገን ነበር፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- አሰልጣኝ ሆናችሁ ቡድኑን ከተረከባችሁ በኋላ ጫናው እንዴት ነው ?

ፋሲል፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ውስጥ ከተጨዋችነት ጀምሮ እዚህ እስክደርስ በጫና ነው ያደግነው፡፡ በተለይም ግን አሰልጣኝ ከሆንን በኋላ ጫናው ይጨምራል ነገር ግን የተለየ ስሜት አይሰማኝም እኔ ሁሌም በጫና ውስጥ ሆኜ ምን ማግኘት እንዳለብኝ ነው የማስበው፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ ፡- ለደጋፊው የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ ?

ፋሲል፡- ከልጅነታችን ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ውስጥ ነን አሁን ስናስበው ትንሽ ቀን ይመስላል ግን ረዥም ነው፡፡ በእነዚህ ግዜ ውስጥ ደጋፊውን ምን እንደሚፈልግ እናውቃለን፡፡ እኛም እንደ አሰልጣኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ አሸንፈን ከስታዲየም እየጨፈረ እንዲወጣ ነው የምንፈልገው፡፡ ደጋፊውንም እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ድረስ በትዕግስት በመጠበቅ እና ከጎናችን በመሆን እና ተጨዋቶቻችንን በማበረታታት የራሱን አስተዋፆኦ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ፡፡

“ ለስርዓት ቅድሚያ እሰጣለሁ” ዘሪሁን ሸንጋታ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔያደር ዶ ሳንቶስን ከመጋቢት 11/2007 ዓ.ም ጀምሮ ማሰናበቱን እና በምትካቸውም የዕርሳቸው ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ሲሰሩ የቆዩትን ፋሲል ተካልኝን በዋና አሰልጣኝነት እንዲሁም ዘሪሁን ሸንጋታን በምክትል አሰልጣኝነት መሾሙን ቅዳሜ መጋቢት 12 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው የልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡

ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ በዋና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና በምክትሉ ዘሪሁን ሸንጋታ እየተመራ ወላይታ ዲቻን በምንያህል ተሾመ፣ ምንተስኖት አዳነ እና በአዳነ ግርማ ግቦች 3 ለ 1 በማሸነፍ የመጀመሪያውን ሶስት ነጥብ ማግኘቱን ምንያት በማድረግ የዚህ ሳምንት የልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡

ዘሪሁን ሸንገታ በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ይሁን እንጂ በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት ህይወቱ ብዙዎች ማሳካት የማይችሉትንና በህልም ብቻ የሚቀሩበትን ጉዞ ማድረግ ችሏል፡፡ በአስራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን መሰለፍ የጀመረው ዘሪሁን ከአስር ዓመታት በላይ በቡድናችን ውስጥ በመጫወትና ለተወሰኑ ዓመታትም በአምበልነት በመምራት ስሙን  በቅዱስ ጊዮርጊስ የታሪክ ማህደር ውስጥ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ፈረንጆቹ የአንድ ክለብ ሰው (one club man) በሚሉት አይነት መልኩ የተጨዋችነት ዘመኑን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ በተከላካይ ቦታ በመጫወት ያሳለፈው ዘሪሁን ሸንጋታ የአሰልጣኝነት ሕይወቱን “ሀ” ብሎ የጀመረውም የቅዱስ ጊዮርጊስን ወጣት ቡድን በማሰልጠን ነበር፡፡

በወጣት ቡድን ደረጃ ስኬታማ የአሰልጣኝነት ጊዜውን ካሣለፈ በኋላ ላለፉት ጥቂት አመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናውን  ቡድን በረዳት አሰልጣኝነት ሲመራ ቆይቶ ከመጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ዋናውን የወንዶች ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ከልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስም በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- የቡድናችንን የመጀመሪያ ዙር አቋም እንዴት ተመለከትከው ?

ዘሪሁን፡- ቡድናችን በመጀመሪያ ዙር ሁለት አይነት መልክ ነበረው፡፡ የመጀመሪያው እና በጥንካሬ የማነሳው ነገር ቡድኑ የአንድነት ስሜት ነበረው ይህ ደግሞ ብዙ ጨዋታዎችን እንዳንሸነፍ አድርጎናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግን ቡድናችን በእንቅስቃሴ የማጥቃት ዘይቤ ላይ ችግር ነበረው፡፡ ሶስታችንም ተነጋግረን ለማስተካከል ስንጥር የነበረው ተጭኖ ተጫውቶ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ለመስራት ነበር፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- ለብዙ ዓመታት ቡድናችን 4 ለ 0፣ 5 ለ 0 የሚያሸንፍባቸው ጨዋታዎች ብዙ ነበሩ አሁን ግን በጣም ቀንሰዋል የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ትላለህ?

ዘሪሁን፡- ይሄ ነው ተብሎ ምክንያት መስጠት አትችልም፡፡ እኔ ስጫወት የነበረ ጊዜም ከዚያም በፊት የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድኖች በአመት ውስጥ በዛ ያሉ ጨዋታዎችን በሰፊ ግብ ልዩነት  ሲያሸንፉ እናይ ነበር፡፡ ወደ ሜዳ ስንገባም ሁሉም ቡድኖች የእኛን ቡድን ፈርቶት ነበር የሚገባው እና ይሄ ነው ልልህ አልችልም፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- ለዘሪሁን ውብ ጨዋታ ማለት ምን ማለት ነው ?

ዘሪሁን፡-  ውብ ጨዋታ ማለት ኳሱን ይዞ አደራጅቶ በሰው ሜዳ ላይ በመጫወትና ኳስን በመያዝ ተጭኖ ግብ ማስቆጠር ለእኔ ውብ ጨዋታ ነው፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡-በታክቲክስ የምትመርጠው አጨዋወት በቁጥር ግለፅ ብትባልስ?

ዘሪሁን፡- በዛውን ጊዜ የራስህ ፍልስፍና ቢኖርም በጨዋታ ላይ እና እንደተጋጣሚህ አጨዋወት የምትቀያይራቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለእኔ ግን ቡድኔ 4-4-2 ወይም 4-3-3 ቢጫወት እመርጣለሁ፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- የፋሲል እና   የዘሪሁንቡድን ይሄ ነው ብለን መቼ እናየዋለን?

ዘሪሁን፡- እንዲህ ብለህ አትገልፀውም እኛ በመጀመሪያው ዙር የነበሩብንን ችግሮች በማስተካከል ላይ ነው ያለነው፡፡ በተለይም እየሰራን ያለነው ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ድረስ ያሉት ተጨዋቾችን በልበ ሙሉነት ወደሜዳ ገብተው እንዲጫወቱ ለማድረግ ነው፡፡ እንጂ የእኛ የራሳችን የምንለው ቡድን ለመገንባት ጊዜ ያስፈልገናል፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- በዚህ ዓመት ካደረግናቸው ጨዋታዎች ላንተ ምርጡ ጨዋታ የትኛው ነው?

ዘሪሁን፡- በ19ኛው የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያው ዙር የመልስ ጨዋታ ኤም.ሲ.ዑልማ ጋር ባህር ዳር ስታዲየም ያደረግነው ጨዋታ ለእኔ ምርጡ ነው፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋች ነበርክ ከዚያ የወጣት ቡድን ከዚያ ረዳት ከሆንክ በኋላ አሁን የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ሆነሀል ጫናው እንዴት ነው ?

ዘሪሁን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ይህንን ሀላፊነት ስንቀበል የመጀመሪያችን አይደለም ከዚህ በፊትም ቡድናችንን በዋና አሰልጣኝነት እንድንመራ ዕድል አግኝተን የተወሰኑ የጥሎ ማለፍ እና የኮን ፌዴሬሽን ጨዋታዎችን በሀላፊነት መርተናል፡፡ ክለቡ ትልቅ ስም ያለው ፣ ብዙ ደጋፊ ያለውና የሰፊ ታሪክ ባለቤት ስለሆነ ጫናው ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ይሄንን ተጨዋችም ሆነን ስለምናውቀው የሚፈጠር አዲስ ነገር የለም፡፡ እኛ ለማድረግ ያሰብነው እኛ ጋር ያለውን ፍላጎት አንፀባርቀን ተጨዋቾች በሙሉ ልብ እንዲጫወቱ ማድረግ ነው፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- በተጨዋችነት ብዙ አሰልጣኞች አሰልጥነውሀል ረዳት አሰልጣኝ የነበርክ ጊዜም ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር የመስራት ዕድሉን አግኝተሀል፣ የትኛው አሰልጣኝ ተፅዕኖ አድርጎብሀል ?

ዘሪሁን፡- እንደተባለው በቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስጫወት የተለያዩ አሰልጣኞች አሰልጥነውኛል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም አሰልጣኞች የተለያዩ ጥሩ ነገሮችን ወስጄያለው፡፡ እንጂ ይሄ አሰልጣኝ በስልጠና ፍልስፍናዬ ላይ ተፅዕኖ አድርጎብኛል ልልህ አልችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ አሰልጣኝ በአካል ብቃት አሰለጣጠን ላይ ጥሩ ሲሆን ይህንን ከሱ ወስጄያለሁ፣ አንዱ ደግሞ ተጨዋቾችን በማስተዳደር ላይ ጥሩ ሲሆን ይህንን ከሌላው አሰልጣኝ ትወስዳለህ፡፡ ስለዚህም ከሁሉም አሰልጣኝ ብዙ ነገሮችን ወስጄያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- በቡድንህ ውስጥ ቅድሚያ ለምን ትሰጣለህ ?

ዘሪሁን፡- እግር ኳስ ስፖርት ነው ስፖርት ደግሞ በስነ-ስርዓት የተገነባ ነው መቼ ማረፍ፣ መቼ መጫወት፣ መቼ ልምምድ መስራት እንዳለብህ ለዚህ ሁሉ ፕሮግራም ያስፈልገዋል፡፡ ውጤት ለማምጣት ከላይ የጠቀስኳቸውን ነገሮች በስርዓት ማክበር አለበት፡፡ ለቡድን ቀዳሚው ውጤት ሳይሆን ስነ ስርዓት (Dispiline) ነው፡፡

ልሳነ ጊዮርጊስ፡- ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን  ይዛችሁ ቀርባችሁ መከላከያን ገጥማችሁ ነበር ? ዛሬስ ምን እንጠብቅ  ?

ዘሪሁን፡- በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዘን ከመለከላከያ ጋር ተጫውተን ነበር፡፡ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተናል፡፡ በዛሬው እለት አላማችን ማሸነፍ እና ማሸነፍ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ባደረግነው ጨዋታ ጥሩ ጨዋታን ብናሳይም በመከላከያ ተሸንፈናል፡፡ አሁን ደግሞ በሌላ ውድድር በወሳኝ ጨዋታ ተገናኝተናል እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ፡፡

“ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት እየተካሄደ የሚገኘው የከረንቦላ ውድድር ዛሬ ግማሽ ፍፃሜ ይደረጋል፡፡”

በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት መዝናኛ ማዕከል በየዓመቱ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ የከረንቦላ ውድድር የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቀጣይ ሳምንት ሚያዚያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበረውን የትንሳኤን በዓል በማስመልከት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዘንድሮም የከረንቦላ ውድድር በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት መዝናኛ ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጀውን የከረንቦላ ውድድር አጠቃላይ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን እንዲዘጋጅ የሚያደርጉት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ገ/መስቀል ናቸው፡፡

የዘንድሮው የከረንቦላ ውድድር የተለየ የሚያደርገው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት መዝናኛ ማዕከል ከሚካሄደው ውድድር በተጨማሪ በቅዱስ ጊዮርጊስ የተጨዋቾች የመኖሪያ ሆስቴል ውስጥ ለተጫዋቾች ብቻ የፋሲካን በዓል በማስመልከት የተዘጋጀው የከረንቦላ ውድድር መኖሩ ነው፡፡ የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች መካከል ከረንቦላ ውድድር ተሳታፊዎች ስምንት ተጨዋቾች ናቸው፡፡ እነሱም ፡- 1 ደረጃ ፡- ሣምሶን አሠፋ፣ ዳዋ ሁጤሣ፣   አሉላ ግርማ፣ደጉ ደበበ  እና 2 ደረጃ ፡- አዳነ ግርማ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ መሀሪ መና፣ፍፁም ገ/ማርያም መሆናቸው ታውቋል፡፡ በሌላ በኩልበቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት መዝናኛ ማዕከል እየተካሄደ የሚገኘው የከረንቦላ ውድድር በሁለት ምድብ ተደልድለው የሚያካሂዱበት ሲሆን ለዚህም በወጣቶች በአራት ምድብ በመከፋፈል አስራ ስድስት ተወዳዳሪዎች እንዲሁም በአዛውንቶች በአራት ምድብ ተደልድለው አስራ ስድስት ተወዳዳሪዎች ተካፍለውበታል፡፡ ከጅማሬው አንስቶ በተወዳዳሪነት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል ትላንት በተካሄደው የሩብ ፍፃሜ ውድድር ላይ ከወጣቶች ምድብ ኤፍሬም ከ ሄኖክ ፣ ቶማስ ከ ሃብታሙ፣ ሚኪያስ ከ ኤርምያስ እና እያሱ ከ በእምነት በሩብ ፍፃሜ ተገናኝተው ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያስገባቸውን ውድድር አካሂደዋል፡፡


በአዛውንቶች ምድብ በአራት ምድብ ተደልድለው ተከፋይ ከሆኑት አስራ ስድስት ተወዳዳሪዎች ለሩብ ፍፃሜ የቀረቡት ስምንት ተፎካካሪዎች ነጋ ከ አፈወርቅ፣ ፍቃዱ ከ የሺጥላ፣ ታዬ ከ ትዝታው እና ሲሳይ ከ አሰፋ ትላንት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ያካሄዱ ሲሆን አሸናፊዎች ለግማሽ ፍፃሜ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ የዘንድሮውን ውድድር ለየት ከሚያደርገው ነገር አንዱ የተሳታፊዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ መገኘቱ ነው፡፡ ይኸው በወጣቶችና በአዛውንቶች መካከል የሚካሄደው የግማሽ ፍፃሜ ውድድር ዛሬ ከ10፡00 ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጽ/ቤት መዝናኛ ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን የደረጃና የፍፃሜ ጨዋታዎች የትንሳኤ በዓልን ዋዜማ ሚየዚያ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋት ጀምሮ የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በአሰልጣኝ በላቸው ኪዳኔ የሚሰለጥነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን በመጀመሪያው ዙር ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች ከአዳማ ከነማ 1-1 ፣ ከሙገር ሲሚንቶ 2-2 ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ 1-1 በአቻ ውጤት ተለይይቶ ኢትዮጵያ  ቡናን 1-0 በማሸነፉ ተጋጣሚዎች ላይ አምስት ግብ አስቆጥሮ አራት ግብ ተቆጥሮበት በስድስት ነጥብ የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን አጠናቋል፡፡


"የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የመጀመሪያ ዙር ውድድሩን አጠናቀቀ "

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው እና የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች የሚካፈሉበት የታዳጊዎች ውድድር የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እድሜአቸው ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ውድድርን ማዘጋጀት የጀመረው በአምናው የውድድር ዘመን ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2006 በተካሄደው የታዳጊዎች ውድድር በሻምፒዮናነት ያጠናቀቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ የታዳጊ ቡድን እንደሆነም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2007 ዓ.ም የታዳጊዎች ውድድርን እያካሄደ የሚገኘው በአዲስ አበባ በሚገኙ አስር ክለቦች በሁለት ምድብ የሚካሄድ ሲሆን እንዲሁም ክልል ላይ ደግሞ በአራት የታዳጊ ክለቦች መካከል እያካሄደ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ተመዝግበው የሚካፈሉት አስር ክለቦች በሁለት ምድብ ተደልድለው ውድድራቸውን እያካሄዱ የሚገኙት ምድብ “ሀ” ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሐረር ሲቲ፣ ኤሌክትሪክ፣ መከላከያ እና ደደቢት ሲሆኑ በምድብ “ለ” ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከነማ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ናቸው፡፡ 

ሉሲዎቹ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ካሜሩን ያመራሉ

  • ሶስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን ተጨዋቾች በቡድኑ ውስጥ ይገኛሉ

ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለምታዘጋጀው ለ11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ለማለፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን(ሉሲዎቹ) ካሜሩን ላይ የ90 ደቂቃ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡ ሉሲዎቹ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ አንድ ለዜሮ መምራት ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስተናገዱት ሁለት ግቦች ሁለት ለአንድ ተሸንፈው የመልስ ጨዋታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ካሜሩንን በአዲስ አበባ ስታዲየም በገጠመው የሉሲዎቹ ስብስብ የመጀመሪያ ቋሚ አስራ አንድ ውስጥ ሁለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን ተጨዋቾች መልካም ተፈሪ እና ፅዮን እስጢፋኖስ የመጀመሪያ የብሄራዊ ቡድን ተሳትፏቸውን አድርገው ምርጥ እንቅስቃሴን አሳይተዋል፡፡ በተለይም የሉሲዎችን የመሀል ተከላካይ መስመር በመምራት ረገድ ምርጥ እንቅስቃሴዋን ያደረገችው ፅዮን እስጢፋኖስ ከእግር ኳስ አፍቃሪው ሙገሳን ተችሯታል፡፡ ከጅማ ዩንቨርስቲ በሜዲካል ላቦራቶሪ የቢኤስ ሲ ዲግሪዋን የያዘችው ፅዮን አስጢፋኖስም «ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄራዊ ቡድን ተጠርቼ ያደረግኩት የመጀመሪያ ጨዋታ ለእኔ ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም ራሴን ለማሻሻል ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብኝ ያየሁበት ጨዋታ ነው፡፡ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ነገር በማድረግ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንጥራለን» በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ 

የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በየ አራት አመቱ በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙ ሀገሮች መካከል ይካሄዳል፡፡ ይህንን ውድድር የሚያዘጋጀው የአፍሪካ ከፍተኛው የስፖርት ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት አካል ነው፡፡ በመጪው መስከረም ወር 54 የአፍሪካ ሀገሮችን በ22 የስፖርት አይነቶች በማወዳደር በሚካሄደው በዚህ ውድድር  ላይ ኢትዮጵያን በእግር ኳሱ ለመወከል ሉሲዎቹ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

አዲስ አበባ መምጣት ስለምትፈልግ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅ ክለብ ስለሆነ ነው የተቀላቀልኩት የምትለዋ ፅዮን እስጢፋኖስ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ የሰራናቸውን ስህተቶች ማረም ከተቻለ ካሜሩንን አሸንፈው ሊያልፉ እንደሚችሉ ትናገራልች፡፡«እንደሚታወቀው እግር ኳስ ጨዋታ ላይ ግብ የሚቆጠርብህ ስህተት ስትሰራ ነው፡፡ ማንም ሰው ስህተት ካልሰራ ግብ አይቆጠርም፡፡ እኛ የሰራናቸው ሁለት ስህተቶች ግብ እንዲቆጠርብን እና ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል፡፡ ስለዚህም በቡድናችን ላይ የታዩትን አንዳንድ ስህተቶች በማረም ካሜሩን ላይ የምናደርገውን ጨዋታ በድል ለማጠናቀቅ እንሰራለን በማለት ገልጻለች፡፡»

ለመጀመሪያ ጊዜ ለሴቶች ብሄራዊ ቡድን መጠራቷን ከመገናኛ ብዙሀን መስማቷንና መደሰቷን የምትናገረው ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴቶች ቡድን አምበል መቅደስ ማስረሻ ናት፡፡«የሉሲ  አባል መሆኔን ያወኩት በኢቢሲ በሚተላለፈው የኢትዮ ሊግ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ መጠራቴን ስሰማ እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ የሁሉም ተጨዋች የመጨረሻ ግብ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ነው፡፡ እኔም በዚህ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሉሲዎቹ በመጠራቴ አመቴን የተሟላ ያደርገዋል፡፡አሁን ደግሞ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት ጠንክሬ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡»

በ2004 ዓ.ም. የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድንን በማሰልጠን በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ውስጥ ስራዋን የጀመረችው አሰልጣኝ ሰላም ዘርአይም የዘንድሮው የሉሲ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ናት፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ  የቅዱስ ጊዮርጊስን ሴቶች ቡድንን ከማቋቋም ጀምሮ በአሰልጣኝነት በመምራት ላይ የምትገኘው ሰላም ዘርአይ አዲስ አበባ ላይ ከካሜሩን ጋር ያደረግነው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የማጣርያ ጨዋታ ትልቅ ትምህርት እንደሰጣቸው እና ካሜሩን ላይ ለሚካሄደው ጨዋታም ውጤቱን ለመቀልበስ ጠንክረው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ለልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ተናግራለች፡፡


የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የባህርዳር ዝግጅት እንዲሳካ አስተዋፅኦ ያደረጉ ደጋፊዎችን አመሰገነ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ሀገራችን ኢትዮጵያን በመወከል በ19ኛው የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ መሳተፉ ይታወሳል፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናን በማስተናገዱ ምክንያት የሻምፒዮንስ ሊጉን የመጀመሪያው ዙር የመልስ ጨዋታችንን በባህር ዳር ከተማ እንድናደርግ ተወስኖ ውድድራችንን ደማቅ በሆነ ሁኔታ አካሂደን መመለሳችን ይታወሳል፡፡

ባህር ዳር ላይ በተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኤም ሲ ኤል ኡልማ ጨዋታ ሁለት አዳዲስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክብረ ወሰኖች ተመዝግበዋል፡፡ የመጀመሪያው ክብረ ወሰን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ አንድን ጨዋታ ከ60000 ህዝብ በላይ በስታዲየም ተገኝቶ ሲከታተለው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኤል ኡልማ ጨዋታ የመጀመሪያው ሲሆን ከዚህ ጨዋታ ስታዲየም መግቢያ ትኬት የተገኘው 680,231 ብር በታሪክ ከፍተኛው ሆኗል፡፡

ይህ ታላቅ ታሪክ እንዲመዘገብ የቅዱስ ጊዮርጊስ የልብ ደጋፊዎች፤የፅህፈት ቤት ሰራተኞች እና የክለባችን ደጋፊ ድርጅቶች ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ አባል ደጋፊዎቻችን ወደ ባህር ዳር የሄዱትን 21 አውቶብሶች ውስጥ የነበረውን ደጋፊ በመመዝገብ እና ከመነሻው ጀምሮ እስከ መድረሻው ድረስ በማስተባበር ልዩ ድረሻን ተወጥተዋል፡፡ የቲኬት ተቆጣጣሪ የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ አባል ደጋፊዎችም ለገቢው መብዛት ከፍተኛ አስተዋፅኦን አድርገዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ባህር ዳር ከተማ ላይ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት፤ በየቤቱ፤ በየመጠጥ ቤቱ፤ በዩንቨርስቲዎች እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ በመገኘት የባህርዳር ህዝብ ስለ ጨዋታው በቂ ዕውቀት እንዲኖረው ብሎም ስታዲየሙ እንዲሞላ የብዙዎችን አፍ ያስከፈተ ታላቅ ቅስቀሳን ያደረጉት የባዛር እና ቅስቀሳ ኮሚቴም ይህ ታሪክ ሲመዘገብ ዋንኛ ባለ ድርሻ አካላት ነበሩ፡፡

ይህንን ትርጉም ያለው እና የሚታይ ስራ በመስራታቸውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ባሳለፍነው ሳምንት  ለሁሉም አስተባባሪዎች ክቡር ፕሬዘዳንታችን አቶ አብነት ገብረመስቀል በተገኙበት የምስጋናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡

"ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ዛሬ በ11፡30 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታል"

የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የመጀመሪያው ዙር ተጠናቆ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች እየተካሄደ ይገኛሉ፡፡ በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ የተጀመረው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር እስካሁን ስድስት ወራትን ያስቆጠረበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተሳተፉ ክለቦች ብዛት አስራ አራት ሲሆኑ ውድድሩም በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተማ ሜዳዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድሩን ፕሮግራም በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የጨዋታ ቀን ለውጥ እያደረገበት መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ በተለይ ለእግር ኳስ ተመልካቹ ለሁሉም ነገር አመቺ በሆነበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በተለያዩ ምክንያቶች የፕሪሚየር ሊጉን ውድድር ስያስተናግድ ከቆየ ወራቶችን አስቆጥሯል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ዙር ውድድር መካሄድ ከጀመረ የ14ኛ፣ የ15ኛ እና የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ጨዋታዎች በተስተናገዱበት የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በ14ኛ ሳምንት ዘጠኝ ግቦች በ15ኛ ሣምንት 22 ግቦች እንዲሁም በ16ኛው ሣምንት 12 ግቦች የተቆጠሩበት ሆኗል፡፡ በተለይ በ15ኛው ሣምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች 22 ግቦች ማለትም በርካታ ኳሶች ከመረብ ያረፉበት እንደሆነም ማወቅ ተችሏል፡፡ በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ቡድኖች በተቀመጡበት የደረጃ ሠንጠረዥ ያስመዘገቡት ነጥብ ተቀራራቢ ሆኖ ይታያል፡፡ በደረጃ ሠንጠረዥ አቀማመጣቸው በመጨረሻ ላይ የሚገኙት ክለቦችም የነጥባቸው አቀማመጥ የተቀራረበ ሆኖ ቢገኝም በ14ኛው ላይ የሚገኘው የወልዲያ ከነማ ቡድን አምስት ነጥብ ላይ መቀመጡ በወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲጠበቅ እያደረገው ይገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በ14ኛው ሣምንት አዳማ ከነማ 2-0 ሲያሸንፍ የመጀመሪያዋን ግብ ብራይን ሁለተኛዋን ግብ ምንተስኖት ማስቆጠራቸው ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ15ኛው ሳምንት ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ወደ ሐዋሳ ተጉዞ ከሐዋሳ ከነማ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2-0 ተሸንፎ ተመልሷል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ16ኛው ሣምንት ጨዋታውን ከወላይታ ዲቻ ጋር በአበበ በቂላ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ 3-1 ሲያሸንፍ የመጀመሪያዋን ምንያህል ሁለተኛዋን ምንተስኖት ሶስተኛዋን ደግሞ አዳነ ማስቆጠራቸው ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይነት በተከታታይ አራት ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያካሂዳል፡፡ የ17ኛው ሳምንት ጨዋታውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በ11፡30 ይጫወታል፡፡ በቀጣይነት በ18ኛው ሣምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና በ19ኛው ሣምንት ከኢትዮጵያ ቡና በ20ኛው ሣምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታውን ካደረገ በኋላ በ21ኛው ሣምንት ከሙገር ሲሚንቶ ከሜዳው ውጭ አሰላ ተጉዞ ጨዋታውን የሚያካሂድ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ተሰናበቱ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ባለው ራዕይ እና በነደፈው እቅድ በአፍሪካ ከሚገኙት ታላላቅ ክለቦች አንዱ ለመሆን እና በውድድር ተሳትፎም በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ስምንት ውስጥ ለመግባት በማሰብ ፋና ወጊ ሆኖ የውጪ ሀገር አሰልጣኝ በማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን መሰረት በማድረግ ብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስን በመቅጠር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዚህ በፊት ከነበረን ተሳትፎ የላቀ ውጤት ለማምጣት እና የተሻለ ደረጃ እንዲያደርሱን በማሰብ ስምምነት ላይ ደርሰን ቀጥረናቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ሆኖም በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏችን በመጀመሪያው ዙር ለመውጣት ተገደናል፡፡አሰልጣኙ ቢጥሩም የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናም እየታየ ያለው እንቅስቃሴ የዋዠቀ እና ተስፋ ሰጪ ሆኖ ባለመገኘቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ ከመጋቢት 11/ 2007 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡

ኔይደር ዶስ ሳንቶስን በመተካትም ምክትል አሰልጣኞቻቸው የነበሩት ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ በዋና አሰልጣኝነት ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያሰለጥኑ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ በቆይታቸው ወቅት ላደረጉት ጥረት ከልብ እያመሰገንን በሚሄዱበት ሁሉ መልካም እድል እንዲገጥማቸው እንመኛለን፡፡